tg-me.com/tikvahethiopia/93391
Last Update:
" አሁን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ማብቃቱ አይቀርም፤ ነገር ግን መች እንደሚያበቃ ማወቅ አይቻልም " - አታላይ አየለ (ፕ/ር)
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ መምህርና ተመራማሪ አታላይ አየለ (ፕ/ር) ምን አሉ ?
" ዛሬ በአፋር ክልል ፥ በዱለቻ ወረዳ በዶፋን ተራራ ላይ የተከሰተው ጭስ እና እንፋሎት የሚመስል ነገር እሳተ ገሞራ ሳይሆን በሙቀት አካባቢ ያለው የእንፋሎት ውኃ በኃይል እየተወረወረ በመውጣቱ የተፈጠረ ክስተት ነው።
በተፈጠረው ሁኔታ እሳት አይታይም ፤ ወደፊት አለት ሊረጭ እንደሚችል አመላካች ሊሆን ይችላል።
ከመስከረም ወር ጀምሮ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንዝረቱ እየተሰማ ነው።
ከሰሞኑን በሬክተር ስኬል ከፍ ያሉ የመሬት መንቀጥቀጦች በፈንታሌ እና ዶፈን አካባቢ ተከስተዋል።
የመሬት መንቀጠቀጡ በተደጋጋሚ መከሰቱ በአካባቢው እንዲሁም ንዝረቱ በሚሰማባቸው አካባቢዎች ጫና እየፈጠረ ነው።
በተለይም በአካባቢው በነበሩ በባህላዊ መንገድ የተሠሩ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
የዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተሰማ ነው። ለዚህም መደረግ ያለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች አሉ። እነዚህም ፦
➡️ ቁምሳጥን ላይ የሚቀመጡ ውድ እና ተሰባሪ እንዲሁም ተቀጣጣይ የሆኑ ዕቃዎችን መሬት ላይ ማስቀመጥ፣
➡️ ቅጽበቱ እስኪያልፍ ማዕዘን አካባቢ መቆም፣
➡️ ጠረጴዛ ስር እና ጭንቅላትን መከላከል በሚያስችል ቦታ መከለል መደረግ ካለባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል ናቸው።
የመሬት መንቀጥቀጥን መተንበይ አይቻልም ያደጉ ሀገራት የጥፋት መጠኑን ሕዝባቸውን በማስተማር እንዲሁም በሕንፃ አሠራር ቴክኖሎጂ መቀነስ ችለዋል።
አሁን ላይ እየተከሰተ ያለው ተደጋጋሚ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ማብቃቱ አይቀርም፤ ነገር ግን መች እንደሚያበቃ ማወቅ አይቻልም ። "
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የኤኤምኤን ነው።
@tikvahethiopia
BY TIKVAH-ETHIOPIA
Share with your friend now:
tg-me.com/tikvahethiopia/93391