tg-me.com/tikvahethiopia/91626
Last Update:
በወላይታ ዞን መምህራን በፖሊስ እየታሠሩ መሆኑን የታሳሪ ቤተሰቦች ለዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ ገልጸዋል።
እስሩ የተፈፀመ ያለድ መምህራኑ ከደሞዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፊርማ በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አቤቱታቸውን ለማስገባት መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።
ፖሊስ መምህራኑን የሚያስረው " አመፅ ለመቀስቀስ ተንቀሳቅሰዋል፤ የዞኑን ገጽታ አጥፍተዋል " በሚል መሆኑን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል።
መምህር ዳንኤል ፋልታሞ በዳሞት ወይዴ ወረዳ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በእንግሊኛ ቋንቋ መምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
መምህሩ በዞኑ ፖሊስ አባላት እስከታሠሩበት እስካለፈው ሰኞ ድረስ የመምህራን ደሞዝ እንዲከፈል ለመጠየቅ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንደነበሩ የሚያውቋቸው የስራ ባልደረቦቻቸው ገልጸዋል።
መምህሩን ሌሊት ፖሊሶች ከቤት ይዘዋቸው እንደሄዱ ነው የ3 ልጆች እናት የሆኑት ባለቤታቸው ለሬድዮ ጣቢያው የጠቆሙት።
ፖሊሶች ሌሊት 9 ሰዓት ላይ ወደ ቤት እንደመጡ የጠቀሱት የመምህሩ ባለቤት " በወቅቱ ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበረም። ቤተሰቡ በሙሉ በእንቅልፍ ላይ ነበር። ቤቱን አስከፍተው ከገቡ በኋላ አልጋ እና ፍራሽ ሳይቀር ፈትሸው ምንም ሊያገኙ አልቻሉም። በመጨረሻም ግን ባለቤቴን ይዘውት ሄዱ " ብለዋል።
ለደህንነታችን ሲባል ስማችን አይጠቀስ ያሉ ሌላ ሁለት የዚሁ ወረዳ ነዋሪዎች ባሎቻቸው ደሞዝ ይሰጠን ብለው የዳቦ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ታሰረውብናል ብለዋል።
" ፖሊሶች ወደ ቤት ሲመጡ ምንም አይነት የፍርድ ቤት መያዣ ወረቀት አላሳዩም " ያሉት የመምህራኑ ቤተሰቦች " የተሳሳተ መረጃ አሰራጭታችኋል " በሚል መያዛቸውን ከአንድ ፖሊስ አባል መስማታቸውን ተናግረዋል።
" የመምህራን ደሞዝ ይከፈል " በሚል የፊርማ ማሰባሰብ ስራ ሲያከናውኑ ከነበሩት መካከል 3 በቅርብ የሚያውቋቸው መምህራን መታሰራቸው የተናገሩ አንድ የዳሞት ወይዴ ወረዳ መምህር አስተባባሪዎቹ ከመታሠራቸው በፊት " እረፉ " የሚል መልዕክት ከወረዳው አመራሮች ተልኮባቸው እንደነበር ጠቁመዋል።
የወረዳው እና የዞን ኃላፊዎች ለቀረበው ክስ ምላሽ አልሰጡም።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል ጳውሎስ ለሬድዮ ጣቢያው ፤ " መምህራን ደሞዝ የመጠየቅ መብት መንግሥትም የመክፈል ግዴታ አለበት። የደሞዝ ጥያቄ በማቅረባቸው እሥርና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል የሚል መረጃ እስከአሁን እኛ አልደረሰንም። ነገር ግን ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ትክክል አይደለም። እኛም የምንታገለው ይሆናል " ብለዋል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ ነው።
@tikvahethiopia