Telegram Group Search
ጥንታዊው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ መቅደስ እየታደሰ ነው፡፡

የእደ ጥበብ ውጤታቸውን ዘመን አላደበዘዘውም:: የብራና መጻሕፍት፣ የብር፣ የነሐስና የብረት መስቀሎች እንዲሁም ሌሎች የዘመንን ድንበር የተሻገሩ የታሪክ አሻራ መንፈሳዊ ቅርሶች ብቻ ሳይሆን የቤተ መቅደሱ ግድግዳ የተገነባበት ዕፅ (እንጨት)፣ ጣራው የተሠራበት የእንጨትና የቃጫ ሥራ ውጤት የእደ-ጥበብ ስልቱን፣ ዲዛይኑን (ንድፉን)፣ ውበቱን፣ ካስቆጠረው ክፍለ ዘመንና ከተሠራበት ቅድመ አያቶቻችን የቴክኖሎጂ ዘመን ጋር ለማነጻጸር መሞከርና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስቸግራል፡፡ ምን አልባት ምክንያታዊ መልስ ሊሆን ከሚችለው አንዱ ተጠየቅ ቅድመ አያቶቻችን “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡” የሚለውን ጥቅስ ከግድግዳ የሚለጥፉ ሳይሆኑ፤ በልበ ሰሌዳቸው ቀርጸው በሕይወት ይኖሩ ስለነበር የስኬታቸው ምሥጢር ይህ ሊሆን ይችላል ማለት ይቀላል፡፡

በሀገር በቀል እውቀትና ቁሳቁስ ከተገነቡትና የጁ አካባቢ ከሚገኙት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ነው፡፡ ትክለ-ዘመኑ ከዘመነ መሳፍንት ይመዘዛል፡፡ ሕንጻ ቤተ መቅደሱ ምዕተ ዓመትን እያስቆጠረ ጉዞውን እንደቀጠለ ነው - በሰሜን ወሎ መንበረ ጰጰስና ሀገረ ስብከት በወልድያ ከተማ አስተዳደር ቤተ ክህነት ስር የሚገኘው የወልድያ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን፡፡ በ፳፻፲፮ (2016) ዓ.ም የሕንጻ ቤተ መቅዱሱን የጣራ ክዳን የመቀየር ሂደት (እድሳት) እየተደረገለት ነው፡፡ የጣራው እንጨት ቁንቁን ሳይደፍረው፣ የቃጫው ስንጥር እንጨት የታሰረበት ልጡ ሳይላላ፣ ሳይበሰብስ፣ ሳይበጠስ አዲስ መልክ፣ አዲስ ይዘት እንደያዘ ምንም ሳይዛባ የፋብሪካ ምርት የሆነው የቆርቆሮውን ክዳን ብቻ እርጅና ዙሮበት፣ መልኩ ዳብሶ፣ ይዘቱ ተዛብቶ፣ ሲቀየር ሌሎቹ አዲስ ሆነው ቀይሩኝ አለማለታቸው የጥንታዊውን ሕንጻ ቤተመቅደስ እደ-ጥበቡ ሳይዛባ፣ ጥንታዊ አሻራው ሳይቀየር እንደነበረ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡

ከሕንጻ ቤተ መቅደሱ በተጨማሪ በውስጡ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶችም ምልክትነታቸው ልዩ ነው፡፡ ታሪካዊ አሻራቸው የዘመን ምዕራፍን እያስቆጠሩ የጥንትን ሥልጣኔ የሚያሳዩ ብቻ አይደሉም፡፡ ብረት ቀጥቅጠው፣ ወርቁን አንጥረው፣ ነሐሱና መዳቡን እንደየ ባሕሪው አዘጋጅተው በራሳቸው ዲዛይን ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጰያዊ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎችን ሩቅ አሳቢነት ምዕተ ዓመታትን ወደኋላ ተጉዘን እንድናስታውስ ያስገድዳል፡፡ ይህ ዓይነት አስረጅ ተከትቦ የሚገኘው ከብራና ጽሑፍ የታሪክ ዓምድ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ከእጅ መስቀል እስከ መጾር መስቀል እንዲሁም ከብር አክሊል ከመሳሰሉ ልዩ ልዩ ቅርሶች ላይ ገንዘቡን ከፍሎ ያሠራውን ወይም ያሠራችውን የተጸውኦ ስም ከእነ ክርስትና ስሙ ወይም ስሟ በተመሳሳይ ሁኔታ የእደ ጥበብ ባለሙያውን ስም ከእነ ዘመኑ የሚገልጸው መረጃ ተጽፎ ይገኝበታል፡፡

ቦታው ላይ የሚገኘው ሌላኛው አስደናቂ የታሪክ አሻራ ዘርፍ መካከል ከነገሥታት መቀጫ ወንበር ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን እንደተሠራ የሚነገርለትና ታላቁ ራስ ዓሊ ጓንጉልም ሲቀመጡበት የነበረው ወንበር ክፍለ-ዘመናት እየተቀባበሉት እንደዘለቀ ነው፡፡ ውጫዊ ገጽታው አልወየበም፣ ከቅርጽ እስከ ውበትና ዲዛይኑ እንዲሁም ከተዛመዱበት የብረትና የእንጨት ቡለን ጋር አለመዛባቱ የአያያዝ ጥንቃቄ ወይንስ የተሠራበት ቁስና የአሠራር ጥንካሬ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

በአጠቃላይ የወልድያ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተ መቅደስ እንደ አንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ቤተ መቅደሱ አማኞች በመስቀሉ ተዳሰው፣ መዓዛ እጣኑን አሽትተው፣ ሥጋ ወደሙን ተቀብለው፣ በእምነቱ ተቀብተው፣ በድርሳኑ ጠበል ተረጭተውና ጠጥተው፣ ሕገ-ልቡናን፣ ሕገ-ኦሪትን እና ሕገ-ወንጌል ተምረው ለስጋ ሥራና ለመንፈስ ሥራ በመትጋት “ለኩሉ ዘስጋ ወለኵላ ዘነፍስ” የሚለውን ሕይወት ለመኖር እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሰውን እንደራሱ የሚወድና የሚያከብር በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ የሚገነባበት በዕድሜና በፆታ ያልተገደበ የትምህርት ማዕድ የሚሰጥበት ጥንታዊና ታሪካዊ መንፈሳዊ ተቋም ነው፡፡

ከእምነት ባሻገር ደግሞ በሌላኛው ክፍሉ ከቤተ እምነት ተከታዮቹ ባለፈ ታሪካዊና ቁሳዊ ሀብቱ ለቱሪዝሙ ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሚያስገኘው ፋይዳ ተጠቃሚው የሌሎችም ቤተ እምንት ተከታይ ሁሉ መሆኑን ማንኛውም የተማረ ሰው የሚረዳው ሀቅ ነው፡፡
በመሆኑም ቤተ መቅደሱንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመንከበካባና በመጠበቅ ለትውልድ ያደረሱ አባትና እናቶቻችን እንዘክር፡፡

እኛም የተረከብናቸውን ቅርሶች ተንከባክበን ለቀጣይ ትውልድ የማድረስ፣ ለጥናትና ምርምር አገልግሎት እንዲውሉ፣ ታሪካዊ ቤተ መቅደስ በመንፈሳዊ ሀብቱና በታሪካዊ አሻራው እንዲቀጥል በየመክሊታችን ቀርበን እንደግፍ፡፡ ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታችንንና ኃላፊነታችንን እንወጣ መልእክታችን ነው፡፡
#የድጋፍ_ጥሪ

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ታላቁ ራስ አሊ በ1770ዎቹ ከመሠረቷቸው አብያተክርስቲያናት መካከል በታሪካዊነቱና በቀደምት ቅርስነቱ የሚታወቀው የወልድያ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አንዱ ነው።

ይህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ጣራው እያፈሰሰ ጉዳት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በባለሙያ ተጠንቶ ሙሉ ጥገና (እድሳት) እንዲደረግለት የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ አዋቅሮ ጥገናው እየተካሄደ ይገኛል።

ስለሆነም የሚመለከታችሁ ሁሉ ይህንን እድሜ ጠገብና ታሪካዊ ቤተክርስቲያን በተቻላችሁ መጠን ከታች በተዘረዘሩት የሕንጻ ቤተክርስቲያን እድሳት ኮሚቴ የሒሳብ ቁጥሮች ድጋፍ ታደርጉልን ዘንድ በኀያሉ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል ስም ጥሪያችንን እናስተላለልፋለን።

የእድሳት ኮሚቴ ሒሳብ ቁጥሮች
ንግድ ባንክ 1000592796655
አቢሲኒያ ባንክ 192626269
አማራ ባንክ 9900026519504
ፀደይ ባንክ 0702160001330

ለበለጠ መረጃ +251919477405 ጸሐፌ ትእዛዝ ምትኩ ገዳሙ (የደብሩ አስተዳዳሪ)
2024/07/20 06:53:54
Back to Top
HTML Embed Code: