Telegram Group Search
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

              #ሰኔ ፲፮ (16) ቀን።

እንኳን #የእግዚአብሔር_መልአክ_ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት #ሕፃኑንና_እናቱንም_ይዞ_ወደ #እስራኤል_አገር_እንዲመለስ_ላአዘዘበት_ዕለትና #መልካም_ሽምግልና_ላለለው ስም አጠራሩ ለከበረ በገዳም ለሚኖርና በገድል ለተጠመደ #ለስልሳ_ዓመት ብቻው ሰው ሳያይ ለኖረ አባት ለላይኛው ግብጽ ሰው #ለአባ_አቡናፍር_ለዕረፍቱ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #የአባ_አቡናፍርን_ገድል ከተናገረ #ከአባ_በፍኑትዮስ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                            ✝️ ✝️ ✝️
#አባ_አቡናፍር፦ የዚህም አባት ገድል የተናገረ አባ በፍኑትዮስ ነበር እርሱ ቊጥሩ ከገዳማውያን ነውና። አባ በፍኑትዮስም ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ዛፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ።

በአንዲት ዕለትም አባ በፍኑትዮስ ወደርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍርን አየው ፈርቶም ደነገጠ የሰይጣን ምትሐት የሚያይ መስሎታልና ይህም አባት አቡናፍር ልብስ አልነበረውም ጸጒሩና ጽሕሙ ሥጋውን ሁሉ ይሸፍናሉ አባ በፍኑትዮስም በላዩ በመስቀል ምልክት አማትቦ አጽናናው በፊቱም አቡነ ዘበሰማያት ጸለየ ከዚህም በኋላ "አባ በፍኑትዮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው" አለው ይህንንም በማለት ከእርሱ ፍርሃቱን አራቀለት።

ከዚህ በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ የእግዚአብሔርንም ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ። ከዚህም በኋላ ወደዚህ በረሀ ከዓለም አወጣጡ እንዴት እንደሆነ በዚያ በረሀ አኗኗሩ እንዴት እንደሆነ ይነግረው ዘንድ አባ በፍኑትዮስ አባ አቡናፍርን ለመነው። አባ አቡናፍርም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እኔ ደጋጎች ዕውነተኞች መነኰሳት በሚኖሩበት በአንድ ገዳም እኖር ነበር የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኑአቸውም ሰማሁ "እኔም ከእናንተ የሚሻሉ አሉን?" አልኳቸው እነርሱም "አወን እነርሱ በበረሀ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን በበረሀ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው" አሉኝ። ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልቤ እንደ እሳት ነደደ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ የፈቀደውን ይመራኝ ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ተነሥቼ ጸለይኩ። ትንሽ እንጀራም ይዤ ተጓዝኩ አንድ ጻድቅ ሰውም አግኝቼ የገዳምውያንን ገድላቸውንና ኑሮአቸውን እያስተማረኝ በእርሱ ዘንድ ኖርኩ።

ከዚህም በኋላ ወደዚህ ደረስኩ እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝን ይቺን ሰሌን አገኘኋት በየዓመቱም ዐሥራ ሁለት ዘለላ ታፈራለች ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚች ምንጭ እጠጣለሁ በዚች በረሀ እስከ ዛሬ ስልሳ ዓመት ኖርኩ ከቶ ያላንተ የሰው ፊት አላየሁም" አለኝ። ይህንንም ሲነጋገሩ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ ወረደ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ሰጣቸው። ከዚያም በኋላ ከሰሌን ፍሬ ጥቂት ምግብ ተመገብን። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ እንደ እሳትም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክኮ ሰገደ ለአባ በፍኑትዮስም ሰላምታ ሰጠው ያን ጊዜም ነፍሱን በጌታ እጅ ሰጠ። ቅዱስ በፍኑትዮስም በጸጉር ልብስ ገንዞ በዚያች ቦታ ቀበረው።

ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ አሰበ በዚያን ጊዜ ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች የውኃውም ምንጭ ደረቀ። ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የቅዱስ አባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ የከበሩ ገዳማውያን በአባ አቡናፍርና በአባ በፍኑትዮስ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 16 ስንክሳር።

                        ✝️ ✝️ ✝️
"#ሰላም_ለአቡናፍር_ጊዜ ተዳደቆ_መዊት። እንተ ተለወጠ ገጹ አምሳለ ውዑይ እሳት። ድኅረ ቀበሮ በፍኑትዮስ በውሳጤ በዓት። ኢትትዋስ ለካልአን ዘተውህበቶ ሲሲት። ነቅዐ ማይ የብስት ወወድቀት በቀልት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሰኔ_16

                         
@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

🕊  † ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ  †  🕊

ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ነው:: ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት:አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር:: ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: በሥርዓት አድጎ: መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል::

ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምሕሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል:: መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር::

ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ: ሲያደንቁዋቸውም ሰማ:: እርሱ በዛ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምሕሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው:: እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚሕ በጣም ርቅው: ንጽሕናቸውን ጠብቀው: ከሰውና ከኃጢአት ተይለው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ" አሉት::

ቅዱስ አቡናፍር "በዚሕ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ:: ዓለም እንኩዋ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም" አሉት:: ይሕንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም::

ከመምሕሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ:: ለብዙ ቀናት ከተጉዋዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ:: ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ::

ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ:: አካባቢው የውሃ ጠብታ የማይገኝበት: ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኩዋ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት: ልምላሜ ሣዕር የሌለበት: ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር:: በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም::

ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር:: ቅዱሳኑን ይሕ አያሳስባቸውም:: ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም: ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና:: አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ:: በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ [በቀልት] በቀለች:: ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ [ንጹሕ ምንጭ] ፈለቀች::

ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ:: ዓመታት አለፉ:: ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ:: በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለ፷ [60] ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ:: የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን [የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው] ላከላቸው::

ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ:: እንደ እሳትም ነደደ:: አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ:: ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ: ሰገዱና አማተቡ:: ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ቅዱሳን መላዕክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጉዋት:: የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይሕን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች: ቅርንጯም ደርቃለች::

ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት::

ከሰው [ ከዓለም ] ርቀው: ንጽሕ ጠብቀው: ዕጸበ ገዳሙን: ግርማ አራዊቱን: ጸብዐ አጋንንትን ታግሠው የኖሩ: ስማቸውን የምናውቀውንም ሆነ የማናውቃቸውን እንድናከብራቸው ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓትና በዓል ሠርታለች::

አምላካችን ከአበው ባሕታውያን ጸጋ በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አባ አቡናፍር ገዳማዊ [ስም አጠራሩ የከበረ:
ሽምግልናው ያማረ አባት]
፪. አበው ቅዱሳን ባሕታውያን [ ዛሬ የሁሉም ቅዱሳን ባሕታውያን [በተለይም የስውራኑ] ዓመታዊ በዓል ነው::

- ከሰው: ከዓለምና ከኃጢአት ርቀው
- ንጽሕ ጠብቀው
- ዕጸበ ገዳሙን
- ድምጸ አራዊቱን
- ግርማ ሌሊቱን
- የሌሊቱን ቁር
- የመዓልቱን ሐሩር
- ረሐቡን: ጽሙን: መራቆቱን . . . ሁሉ
ስለ ፍቅረ-ክርስቶስ ሲሉ ታግሠውታልና::

"ዛሬም በየበርሃው የወደቁ: ስለ ዓለም ምሕረትን
የሚማጸኑ አሉ::"

አምላካቸው በረከታቸውን ያድለን።

፫. የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ከግብጽ እንዲመለስ የነገረበት [ተዝካረ ሚጠታ ለእግዝእትነ ማርያም]
፬. አፄ ይኩኖ አምላክ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩፡ ኪዳነ ምሕረት ማርያም
፪፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ
፫፡ አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፬፡ ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሠ ሮሜ
፭፡ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፮፡ ቅዱስ ሐርቤ ንጉሠ ኢትዮጵያ

" . . . ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ: ከዚሕም በላይ በእሥራትና በወኅኒ ተፈተኑ . . . ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: ዕብ.፲፩፥፴፮] (11:36) "

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                       †                       

[ ይህም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው።  ]

†   🕊   †    🕊   †

💖

❝ ይህም ለሐዋርያት የተሰጠ በሁለተኛው ልደት ፣ ከእነርሱ በተወለዱት ክርስቲያኖች ሁሉ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ነው። እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ከቤተክርስቲያን ማኅበር [ አንድነት ] አይለይም።

ይህም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው። በክርስትናው ዕለት ጥምቀት በሚጠመቁት ሁሉ ላይ የሚያድርም እርሱ ነው። ክርስቲያን የሚሆኑትም በአንዲት የሐዋርያት ጉባኤ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ብሎ ካህኑ እፍ ባለባቸው ጊዜ ነው። ያን ጊዜም መንፈስ ቅዱስ በተጠመቁት ሁሉ ላይ በርግብ አምሳል ያድራል።

ይህም በተጠመቀበት ዕለት በጌታችን ላይ በርግብ አምሳል የወረደው ፣ በራሱ ላይም የተቀመጠው ፣ በነቢያት አንደበትም የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው። ❞

[ ርቱዓ ሃይማኖት  ]

🕊

❝ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት በእኛ ውስጥ ሳያድር በፊት እግዚአብሔር አብን አባት ብለን መጥራት አንችልም ነበር። ስለዚህም በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን ያልተቀበሉ እርሱን አባት ብለው መጥራት እንዳይችሉና " አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ... " ብለውም መጸለይ እንዳልተፈቀደላቸው እንገነዘባለን። ለዚህ እንዳይበቁ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ምክንያት በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ ባለማደሩ ነው። ❞

[ ፊልክስዩስ ]

†   🕊   ክብርት ሰንበት   🕊   †

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

❇️አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ❇️

=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም
ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ
እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡

+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ
ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን
በፍትሕ
እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::

+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው::
ላኪው አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ
ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::

+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው
ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ
ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::

+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው
አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ
መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና
ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል
ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::

+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው
አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን
"ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል"
ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር)
ተጠራርጎ ሸሸ::

+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)
አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም
"አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡

+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና
ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::

+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ
ተአምራትን ሰርተዋል:-

1.ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ
ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2.ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን
አቁመዋታል::

+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ
እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው
ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ
ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡

✞ አባ ለትጹን የዋህ ✞

=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን
በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን
የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::

+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው
ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት
ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ
የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል
ደረሱ::

+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ
ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት
የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ:
አልምረውም" አላቸው::

+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ::
አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን
መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ:
ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት
አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል
አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ
እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::

+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ
ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::

✞ አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞

=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ
አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት
ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60
ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው
አላየም::

+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል::
በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል::
እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና
በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::

=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት
ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::

=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::ቅዱሳኑንም
አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን
ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::የጻድቅ አፍ ጥበብን
ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::የአምላኩ ሕግ በልቡ
ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                          †                           

🕊        †      የጽድቅ በር     †        🕊

💛

[   እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው .... ! ]

..............................

❝ የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፡ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ ፡ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡

የነፍስን ፆር [ ከዲያብሎስ የሚከፈትን ውጊያና የስጋ ፈቃድን ] ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡ ❞

[  ቅዱስ ዮሐንስ ሃፂር  ]

†   🕊              †                🕊   †

አንድ ወንድም ገና በጧቱ ራበውና ከሦስት ሰዓት በፊት ላለመብላት ከፍላጎቱ ጋር ታገለ፡፡ ሦስት ሰዓት ሲሆን ደግሞ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ልቆይ ብሎ ራሱን አስገደደ፡፡ ስድስት ሰዓት ሲሆን ዳቦውን ቆርሶ ሊበላ ተቀመጠ ፤ ሆኖም "አይ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ልቆይ" አለና እንደገና ተነሣ፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጸሎት ሲያደርስ የዲያብሎስን ኃይል ከእጁ ሥራ ላይ [ ይሠራ ከነበረው ነገር ላይ ] እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው ፣ ረሃቡም ጠፋ፡፡"

[ ከበረሐውያን ሕይወትና አንደበት   ]


         †              †               †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊     ጾ መ ሐ ዋ ር ያ ት     🕊

▷  ❝  በዚያ ጊዜም ይጦማሉ ❞

[   " በመ/ር አምኃ በላይ ... ! "   ]

[                       🕊                       ]
-----------------------------------------------

❝ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን ? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል ፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።

በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም ፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና ፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።

በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም ፤ ቢደረግ ግን ፥ አቁማዳው ይፈነዳል ፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል ፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ❞

[ ማቴ . ፱ ፥ ፲፭ ]


🕊                        💖                     🕊
                             👇
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
2024/06/25 00:21:36
Back to Top
HTML Embed Code: