Telegram Group Search
የ መጽሐፉ:- ስም ሰንፔር
ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ
ገጽ 132
ዋጋ 170 ብር
ቅናሽ 20 % 135 ብር
አከፋፋይ ቤርያ መጻሕፍት መደብር
አድራሻ አ/ አ አራት ኪሎ አርበኞች ሕንፃ ሥር
በቶሎ የራስዎ ያድርጉ!
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (36)

21. አመስግን - ውለታ አይለፍብህ

ይህች ዓለም ለብዙ ሰው ከባድ የትግል ሜዳ ብትሆንም ለአመስጋኞች ግን ቀላል ናት ። ስናመሰግን ችግሩን ሳይሆን እግዚአብሔርን እናያለን ። ስናመሰግን ያጣነውን ሳይሆን ያተረፍነውን እናስባለን ። ስናመሰግን የሄደውን ሳይሆን ያለውን እንመለከታለን ። ማመስገን ዓይንን ያበራል ። ማመስገን ሁሉንም ነገር በዜሮ ከማባዛት ያድናል ። ማመስገን ከተራራው ጀርባ ያለውን መስክ ፣ ከዋሻ መጨረሻ ያለውን ቀና ማለት ያስተውላል ። ማመስገን ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነው ። ማመስገን እኔ ለእኔ ከመረጥሁት እግዚአብሔር ለእኔ የመረጠው ይበልጣል ብሎ መቀበል ነው ። ማመስገን አለማጣት ፣ አለመታመም ፣ አለመጎዳት አይደለም ። ደግ ደጉን የመቁጠር የሕይወት ጥበብ ነው ። የሚያመሰግኑ ሰዎች ልባቸውና ፊታቸው ይበራል ። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ፈተና ይቀይራል እንጂ በቅድሙ ወጥመድ ላይ አይዘገይም ። ሰዎች እኛን የሚፈልጉት ብሩህ ፊታችንን ፣ ቅን ልባችንን በማየት ካለባቸው ችግር ለማረፍ ነው ። ምሬተኛ ስንሆን ሰላማቸውን ላለማጣት ይሸሹናል ። አሊያም ተጠንቅቀው ይቀርቡናል ።

የምናማርረው ምናልባት ችግርን በችግር ለመፍታት ተነሥተን ስላልተሳካልን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ከመንቀሳቀስ ተአምር በመጠበቅ ደክሞን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ትልቅ የምንለውን ነገር ጠብቀን ለዛሬ በሚበቃን ትንሽ ነገር ስላልረካን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ከሰው የመላእክትን ግብር ጠብቀን ሊሆን ይችላል ። ማመስገን ሁሉንም ነገር በልኩ የማየት ውጤት ነው ። የምንፈልገውን ብናገኝም ሞት አይቀርም ። ከሞት የሚያድነው ግን አሁንም በእጃችን ነው ። በሕይወት ውስጥ አለኝ ከማለት አለሁ ማለት ይበልጣል ። የሚጎድልበትም በሕይወት ያለ ነው ። የለኝም ያልነው በሕይወት ስላለን ነው ።

ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ ነው ። ተኝተን የምንነቃው ጠባቂ ወታደር ስላለ ሳይሆን እግዚአብሔር በመንበሩ ስላለ ነው ። ዛሬን ያየነው ወጥተን የገባነው ፣ ዘርተን ያጨድነው ፣ ወልደን የሳምነው በእግዚአብሔር ቸርነት ነው ። ካሉት የሞቱት ቆንጆዎችና ጠቢባን ይበዛሉ ። በዚህ ቀን እንኳ ብዙ ደጋግ ሰዎች ይሞታሉ ። ክፉዎች ለጉድ ይቀመጣሉ ። ሞት በመንፈሳዊ ቋንቋ ምሕረት ነው ። እስረኛ በምሕረት ሲለቀቅ ደስ እንደሚለው በሰማይም የተጠራች ነፍስ በነጻነትዋ ደስ ይላታል ። ግን እስር ቤት ሰብሮ የወጣ ቅጣቱ ከባድ ነው ። እንዲሁም ራሱን ያጠፋ በሰማይ ስደተኛ ነው ። የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ነውና ። እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ ነው ። የዛሬው ስኬትህ ትልቅ ሰው የሆንህና አምላክ አያስፈልግህም የሚል እሳቤ አምጥቶ ከሆነ በጣም ልትጠነቀቅ የሚገባው ሰዓት ነው ። ምክንያቱም ቀጥሎ የሚመጣው ብልሽት ልክ የለውም ። ሰው መታበይ ሲጀምር ውድቀቱ በቅርብ ርቀት ላይ ነው ። እግዚአብሔር ትዕቢትን ፈጥኖ ይቀጣል ። ናቡከደነጾር በተመካበት ቅጽበት እንደ እንስሳ ሆነ ። ሄሮድስ ድምፁ የአምላክ ነው ሲሉት ስለሞቀው ወዲያው ተቀስፎ ሞተ (ዳዳ. 4፡30 ፤ የሐዋ. 12፡23)።

ብዙ ሰዎችን እንታዘባለን ። የእግዚአብሔርን ደጅ በእንባ ያጣበቡትን ሰዎች እናስታውሳለን ። የያዙትን ነገር በትክክል መጨበጣቸውን ሳያረጋግጡ እግዚአብሔርን ትተዋል ። ከቤቱ ርቀዋል ፣ ጸሎት አቁመዋል ። ለምን ሲባሉ ደርዘን ምክንያት ይደረድራሉ ። በምናመሰግንበት ቀን ከሀዲ መሆን ከባድ ኃጢአት ነው ።

ማመስገን አለብን ። በልጅነታችን በጣም የሚወዱን ፣ ይከብደዋል እያሉ የእኛን ሸክም የሚሸከሙልንን ፣ ትምህርታችንን ለማገዝ የሚያስጠኑንን ፣ ከረሜላ እየገዙ የሚስሙንን ፣ እናታችን ገበያ ስትወጣ የሚጠብቁንን ፣ ያሳደጉንን ሞግዚቶች ፣ ስለ እኛ ከሰዎች ጋር የተጣሉንን ተቆርቋሪዎች ዛሬ ማመስገን አለብን ። አዎ እኛ አድገን ሠላሳ ዓመታችን ነው ። እነርሱ ሃምሳ ገብተዋል ። ደግሞም ወልደው ከብደዋል ። ረስተውናል ። እኛ ግን አስታውሰን ምስጋና ማቅረብ አለብን ። ዕድሜ የሚሰጠን የምስጋና ዕዳችንን እንድንከፍል ነው ። እነዚያ ስንራብ ያጎረሱንን ፣ ከቤት ወጥተን ስንከራተት ያስጠጉንን ላንቀየማቸው መውደድ አለብን ። በሰማይ ስንሄድ ከሚያስፈሩ ጥያቄዎች አንዱ በጎ የዋሉልንን አለማመስገን ነው ። እነዚህ ሰዎች ዕድሜ ተጭኖአቸው ፣ ሁሉም ነገር ከብዷቸው ሊሆን ይችላል ። ያኔ በልጅነታችን ለእኛና ለቤተሰባችን ያደረጉትን ስንነግራቸው ደስ ይላቸዋል ። ደግሞም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ስጦታችንን መስጠት አለብን ። ሁሉን ላፌ አይባልም ፣ የተሰጠን ልንሰጥም ነው ። እነዚህ ሰዎች የማይታወሱን ከሆነ አውሬ ነን ። እነዚህ ሰዎች የሚታወሱን ከሆነ አእምሮአችን ባለ ዕዳ ነው ። ከዕዳ ጋር መዋል ፣ ማደር ራስን በሰንሰለት አስሮ መግረፍ ነው ። ዛሬ ማታ ባለውለታዎቻችሁን አስታውሱ ። ያለፈውን ነገር አስታውሳችሁ ንገሩአቸው ። አመስግኑ ። አመስጋኞች ዕድሜአቸው ረጅም ነው


አንተ ግን ስሟ የእንጀራ እናት ቢባልም በጣም ትወድህ የነበረችውን አሳዳጊህን አስብ ። ዛሬ እናትህን በማግኘትህ እርስዋን አትርሳ ። ሲመሽ ምን ሆነህ ነው ያሉህን ፣ ለመሸጥ ካስቀመጡት ዳቦ እየሰጡ ያሳደጉህን እማማ እገሌን ፈልጋቸው ። ጀንበራቸው ልትጠልቅ እያዘቀዘቀች ነውና ቶሎ ብለህ ውለታህን መልስ ። እኒያ የሚወዱህ መምህር ፣ ከዚያ ሁሉ ተማሪ ላንተ ፍቅር ነበራቸው ። እርሳቸው ናቸው አስተማሪ ጥሩ ነው ብለህ እንድትደመድም የረዱህ ። ዓለምን በበጎ ያሳዩህን ፣ የፍቅር መምህሮችህን ፣. የጠዋት ወዳጆችህን ፣ ገና ነፍስህን ሳትረዳት ያፈቀሩህን ፣ ራስህን መውደድ ሳትጀምር አንተ የእኔ ነህ ያሉህን አመስግን ። ስለ አንድ አምላክ ብለህ ምክሬን ስማ ። ራስህን ከታላቅ ጸጸት ትፈታታለህ ። እኔ ቀኑን እየተሻማሁ ነው ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን የወሰዱኝን ፣ ስማር ደብተር የገዙልኝን እያሰስሁ ነው ። አንዳንዶቹ ሞተዋል ። ልጆቻቸው ምስጋናውንና ውለታውን ለመቀበል እየጠበቁኝ ነው ። ግድ የለም የእኔን ልምድ ተወዉ እባክህን አመስግን ። ሰው ሐውልት አይደለም ቆሞ አይጠብቅህም ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.
Audio
የማርቆስ ወንጌል ትርጓሜ 24

ማር.5፥ 35-43

በ#ዲያቆን #አሸናፊ #መኮንን የተዘጋጀ ስብከት
ንባቡ ተጀምሯል !
ውድ ወዳጆች !

የትውልዳችንን ውጥረት ታሳቢ በማድረግ በሳምንት አንድ ቀን የስልክ የማማከር አገልግሎት ለመጀመር እናስባለን ! ምን ይመስላችኋል ?
እግዚአብሔር ይናገራል 6

በ#ዲያቆን #አሸናፊ #መኮንን የተዘጋጀ ስብከት

አሁን በቴሌግራም ቻናል ይለቀቃል ። ይከታተሉ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ትምህርቶችና ስብከቶች ለመከታተል ከሥር የተቀመጡትን ገጾች ይመልከቱ፡-

https://www.tg-me.com/Nolawi ኖላዊ/com.Nolawii

https://www.tg-me.com/nolawisebketoch

https://www.facebook.co m/ashenafi.mekonnen.357

https://youtu.be/3qfQp9yYmHY

www.ashenafimekonen.com
Audio
እግዚአብሔር ይናገራል 6

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
አንተ እኮ !!!

ከለምለም ቅጠል በላይ ደስታዬ ፣
ከሚፈልቀው ይልቅ እርካታዬ ፣
ከመንገድ በላይ መድረሻዬ ፣
የዕለት የዘለቄታ ሳይሆን የዘላለም ማረፊያዬ ፣
በመቃብሬ ላይ ይነሣል ብላህ የጻፍህ ፣
የተጠላሁትን ያፈቀርህ፣ የሰይጣን መልክ ሲሰጡኝ መሳይ ልጄ ያልከኝ ፣ የተነቀፍሁትን ያመንከኝ፣ ወርቅህን እኔ ጭቃው ላይ የጣልህ ፣ መክሊትህን ለአባካኙ የሰጠህ ፣ ጸጋህን ለተራቆተው የናኘህ ...

አንተ እኮ እግዚአብሔር ... ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም.
አሳስብ

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

በግን አንድ ጊዜ ብቻ የሚመልስ እረኛ የለም ። አገልጋይም ደጋግሞ ምእመናንን ከጥፋት መንገድ መመለስ ይገባዋል ። ለመጨረሻ ጊዜ ስህተት የፈጸመ ሰው በዓለም ላይ የለም ። የሰው ልጅ በመውደቅ ሰውነቱን ፣ በመነሣት መንፈሳዊነቱን ይገልጣል ። የአንድ ጊዜ ዕድል መስጠት አማኝን ላያበዛ ይችላል ። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በትዕግሥት እውነትን ማስተማር ፣ ደጋግሞ በመጮህም ምእመናንን ከገደል መመለስ ያስፈልገዋል ። የሚማር ሰው ሁሉ በየትኛውም ዕድሜ ቢመጣ ልጅነት ይታይበታል ። ትምህርት ልጅ ያደርጋልና ። አገልጋዩ ግን የቤቱን ጉድለት ትቶ ፣ የራሱን መጎዳት ረስቶ ቢያገለግልም አሁንም መታገሥ ያስፈልገዋል ። እውነተኛ አገልግሎት ያልተቀበሉትን መስጠት ነው ። ፍቅርን ከሰዎች አላገኘ እንደሆነ ፍቅርን መስጠት ፣ ማንም በውድቀቱ አላዘነለት እንደሆነ ለወደቁት ማዘን የአገልጋይ ወጉ ነው ። የአገልግሎት ፍጻሜው ሰማይ ነው ። ከሰማይ የመጣውን አደራ በሰማይ ያስረክባል ። አገልግሎት አልተመቸም ፣ ሰሚም አልተገኘም ተብሎ የሚቆም አይደለም ። እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ሰው ባይሰማ “ሰማያት ስሙ ፣ ምድርም አድምጪ” ተብሎ የሚጮሁበት ነው (ኢሳ. 1 ፡ 2) ።

ወጣቱ አገልጋይ ማሳሰብ አለበት ። በዕድሜ የገፉ በትክክል መያዛችንን እስኪያረጋግጡ ይደጋግማሉ ። ወጣቱ ግን ይሰለቻል ። በመደጋገም ውስጥ መስማት አለ ። ሰዎች በተለያየ ነገር ልባቸው ይሰረቃል ። እውነቱን እውነት ብለው ለመቀበል ይዘገያሉ ። ያልተቀጡ ኀጥአንን ፣ በመከራ የሚያልፉ ጻድቃንን በማየት “መታዘዝ ምን ጥቅም አለው ” ይላሉ ። ቃሉን ከራሳቸው ፣ በዙሪያቸው ካለው ዓለም ጋር በመታገል ይሰማሉ ። ሰይጣን ቃሉን እንዳንሰማ በመጀመሪያ ፣ እንዳንታዘዝ በመቀጠል ፣ በመጨረሻም ልበ ደንዳና እንድንሆን ይዋጋል ። ማሳሰቢያ የሚል ቃል ያስደነግጣል ። ማሳሰቢያ ቀጥሎ ውጤት ላለው ነገር የሚታወጅ ነው ። እግዚአብሔርን ማሞኘት የሚችል የሚመስለው ሰው አለ ። እርሱ የወደደውን አምላኩ የሚወድለት አድርጎ የሚገምትም አያሌ ነው ። ሲደጋግመው ስህተት ትክክል የመሰለው አለ ። ስላልተቀጣ እግዚአብሔር የፈቀደለት የሚመስለውም አይታጣም ። በነፍሱ እልህ ገብቶ በኃጢአት ጭቃ የሚቦካ አለ ። አንድ ቀን እመለሳለሁ ብሎ ኃጢአት እስከ አንገቱ ደርሶም የሚቀልድ አለ ። ማሳሰብ ግን ያነቃል ። ማሳሰብ በጋራ የማሰብ ውጤት ነው ። አስቤበታለሁ አስብበት ማለት ነው ። አንድን ጥፋት ከሁለት ወገን ማየት እርሱ ማሳሰቢያ ይባላል ። ለዚያ ሰው ማሰብ የሚጠቅመው ሰውዬው ለራሱ ሲያስብ ብቻ ነው ። ሰውን በግድ የሚያድን ፣ በግድም የሚያስኰንን ኃይል በሰማይም በምድርም የለም ።

ተረቶችና የሰው ልጅ ምናባዊ ፈጠራዎች የሚያስደስት ትርኢት አላቸው ። ነገር ግን መጨረሻ የላቸውምና ተስፋ አይሰጡም ፣ ልብን አያሳርፉም ። የክርስትና ሃይማኖት የመጽሐፍ ሃይማኖት ነው ። ሳይንሳዊ ማረጋገጫና ሰዋዊ መላዎች ድጋፍ አይሆኑትም ። ሁሉን ስለደገፈው ጌታ የምንማርበት ነው ። ክፉ ትምህርቶች በዓለም ላይ ተዘርተዋል ። እነዚህ የማይታዩ ማሰሪያዎች ናቸው ። ወጣሁ ሲሉ እንደ አረንቋ ብዙዎችን የሚይዙ ናቸው ። የክፉ ትምህርት አባቱ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው ። ትክክለኛ ያልሆነ አስተሳሰብ የተበላሸ ኑሮን ይፈጥራል ። ወጣቱ አገልጋይ እንደ ሎጥ ሚስትና ልጆቹንም ሳይቀር እየሄደ ማሳሰብ እንጂ ቆሞ መጥራት አይገባውም ። የቆሙ ሰዎች ሌላውን ለማቆም ብቁ ናቸው ። እንቅፋት የሚባለው ቆሞ የቀረ ፣ ወይም ወድቆ የቀረ ፣ የራሱ ባልሆነ መንገድ ላይ የተገኘ ነው ። ቆመን ስንቀር ፣ ወድቀን ስንቀር ፣ የራሳችን ባልሆነ መንገድ ላይ ስንገኝ እንቅፋት እንሆናለን ።

ይመስለኛል ፣ ሊሆን ይችላል ፣ እንደ እኔ አተያይ ፣ እገሌ እንደሚያምነው ተብሎ ሃይማኖት አይሰበክም ። ሃይማኖት እርግጥና በራሱ በሚታመነው በክርስቶስ የተሰበከ ነው ። ያለ ዲሲፕሊን ክርስትናን ማካሄድ ፣ አገልግሎትን ባለ አክሊል ማድረግ አይቻልም ። የአመጋገብ ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ፣ የሰው ለሰው ግንኙነት ፣ የሥራ ፣ የአስተዳደር ዲሲፕሊን ያስፈልጋል ። አገልጋዩ ረጅም ርቀት ለመጓዝም ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በልክ ሊያደርገው ያስፈልጋል ። በቂ ስፖርት የሚሠሩ ተራራውን ለመውጣት ይችላሉ ። አብነት የሚያደርጓቸው ሰዎችም አሉ ። እግዚአብሐርን መምሰል ግን ከደብረ ጽዮን ፣ ከማይፈርሰው ከተማ ያደርሳል ። የሁለት ዓለም ወራሽ የሆነውን ሰው ማገልገል መታደል ነው ። ከኋላው ጥሎት የሚሄደው ሥራ ፣ ከፊት የሚቀበለው እምነት እንዲኖረው አበክሮ ማስተማር የወጣቱ አገልጋይ ድርሻ ነው ። እምነት ብቻ በቂ ነው የሚሉ ሰነፎችን ፣ በምግባሬ እድናለሁ የሚሉ ትዕቢተኞችን መገሠጽ አለበት ። በሥጋና በነፍስ ተዋሕዶ የቆመ ሰው ፣ በእምነትና ምግባር ተዋሕዶም የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ። ማጥፋት እየቻለ የታገሠውን አምላክ እያሰበ ስድብን በደስታ መቀበል እግዚአብሔርን መምሰል ነው ።

የሮማ ጎዳናዎች እንደ ጥንቱ ድምቀት አልታየባቸውም ። ሮም በብዙ ንጹሐን ደም የተጠመቀች የግፍ ከተማ ናት ። ዓለም ሁሉ ሮም እንድትሠራ አዋጥቷል ። የጳውሎስን ቤት ለማግኘት ስዳክር እኔ ጢሞቴዎስ በልቤ ወጣቱን አገልጋይ እንዲህ ስል መከርኩት፡-

“ወዲያው ልታደርገው ያለህን ፈጥነህ አድርግ ፣ ጊዜ የሚሰጠውን ቀጠሮ አብጅለት ፣ ልታደርገው የማይገባህም ለዘላለም አታድርገው ። ቆርጦ መነሣትህ እንጂ ሺህ ጊዜ ማሰብህ ድል አድራጊ አያሰኝህም ። የፈጸምከው ካለ ሌሎች የጀመሩት ነውና ክብር ስጣቸው ፣ የጀመርከው ካለ ሌሎች የሚፈጽሙት ነውና ተተኪዎችን አፍራ ። የዘለቁ ራእዮች ፍቅር ፣ ትሕትናና መንፈሳዊ ቆራጥነት ያለባቸው ስለሆኑ እነዚህን አጥብቀህ ያዝ ። ያጣኸው የሚገኘው የያዝከውን በትክክል ስታየው ነው ። ተፈጥሮ ሁሉ አንተ ብቸኝነት እንዳይሰማህ የከበበህ ቤተ ዘመድህ ነው ። ከሁሉ በላይ የሚራዱህ ቅዱሳን መላእክት አሉና የሚዋጉህን አጋንንት አትፍራ ። የሚያበረታ ጸጋ ፣ የሚያረጋጋ ሰላም ካንተ ጋር ይሁን ! አሜን!

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 19
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም.
ወዴት ነህ ?

ወዴት ነህ ? ብለህ አዳምን የፈለግህ ፣ ያለበትን እያወቅህ ያለበትን ያሳወቅህ ፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በለቢሰ ሥጋ ወዴት ነህ ? ብለህ የፈለግህ ፣ ከገነት ጫካ እስከ ቀራንዮ የጠፋውን ያሰስህ እኛም በተራችን እንጠይቅህ ወዴት ነህ ?

ለመቆምም ለመሄድም ስንፈራ ፣ ለመግጠምም ለመለያየትም ስንሰጋ ፣ ለመጀመርም ለመጨረስም ስንንቀጠቀጥ ፣ መንፈስህ የራቀን ይመስለናል ። እባክህ ወዴት ነህ ? ገጻችን ሲጠቁር ፣ የልጅ አዋቂው ፊት ትካዜ ሲይዘው ፣ የመኖር መላ ጠፍቶ ሞት እንደ መፍትሔ ሲፈለግ ፣ ድሀ ያለችውን ሲነጠቅ ፣ የፈሩት እየደረሰ ፣ የጠሉት ሲወርስ ምነው አንድዬ ጨከነብን ይሉሃል ። እባክህ ራስህን ግለጥ ፤ ወዴት ነህ ? ሳትለየን የተለየኸን ፣ አጠገባችን እያለህ የራቅኸን መስሎ ሲሰማን ወዴት ነህ ? ብለን በተራችን እንጠይቅሃለን ።

መልሱ ጥያቄ ከሆነብን ጥያቄው ምን ሊመስል ነው ? ሽማግሌው በሰላም ማረፍ ፣ ሬሳው አፈር መልበስ ፣ የወጣው መግባት ፣ የተማረው ማምረት ፣ የሠራው ማግኘት ሲሳነው ወዴት ነህ? እንልሃለን ፣ ለመብላት ይከፍለው የሌለው በሰው እጅ ታግቶ ለመኖር ሲከፍል ፣ ፈጥሮ ላልፈጠረ ተወን እንዳትባል እባክህ ወዴት ነህ ? ዓለም ሰላም ሆኖ እኛ ብቻ የታወክን መስሎ ይሰማናልና እባክህ እንፈልግህ ወዴት ነህ ?

የክፋት አማካሪዎች ምድሩን ሞልተውታል ። ገላጋይ ጠፍቶ ቤተሰብ ያልቃል ። አሸናፊ በሌለበት ወንድማማች ይቀላላል ። ከሚደነቅ ወደሚያደቅ ምዕራፍ ስንሸጋገር ፣ ቀኛችን ግራ ሁኖ ግራ ሲያጋባን ወዴት ነህ ? እንልሃለን ። የጠፋውን አዳም ፈልገህ ያገኘኸው ፣ የጠፋብንን እውነት ፈልገን እስክናገኘው እርዳን ። እየጸለይን ካለመሰማት ፣ ስምህን እየጠራን ከመለያየት እባክህ አድነን ። አሁንም በቀረችው ትንሽዋ አቅማችን ወዴት ነህ ? እንልሃለን ። ስለ ድሆች እንባ አለሁ በለን ።

ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም.
ማስገንዘቢያ

ቤርያ መጻሕፍት መደብር በአርበኞች ሕንፃ ላይ የነበረውን ሥራ አቁሟል :: ቀጣዩን አድራሻ እስክናሳውቅ መጽሐፍ የምትፈልጉ በቀጣዩ ስልክ ተጠቀሙ

0910531997

ከአክብሮት ጋር !
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (38)

22. ልጆችን በሥርዓት አሳድግ

ምናልባት እኔ ልጅ የለኝም ይህ ምክር እኔን አይመለከተኝም እያልህ ይሆናል ። ልጆች ከእግዚአብሔር የምንቀበላቸው እንጂ የምንቀማቸው አይደሉም ። ሴት ልጅም የልጅ መንገድ እንጂ የልጅ ፈጣሪ አይደለችም ። መውለድ ጸጋ እንደሆነ አለመውለድም ስጦታ ነው ። አብርሃምና ሣራ እስከ መቶ ዓመት ልጅ አልወለዱም ። እግዚአብሔርን በአንድ ልብ ሁነው ለዘጠናና ለመቶ ዓመት ካገለገሉ በኋላ እግዚአብሔር ልጅ ሰጣቸው ። ልጅ የተቀበሉበት ዓላማም የመሢሑን መምጫ መንገድ ለማሳለጥ ነው ። በሌላ አነጋገር ልጅን ለክርስቶስ ወለዱ ። ለጧሪ ለቀባሪ ሳይሆን ልጅን ለሃይማኖት ወለዱ ። እኛ በልጆቻችን ላይ ካለን ዕቅድ እግዚአብሔር በልጆቻችን ላይ ያለው ዓላማ ይበልጣልና ። ነቢይት ሃና ብዙ ዘመን ልጅ በማጣት አልቅሳለች ። በእግዚአብሔር ቤት ባሉ ምእመናን መሳለቂያ እስክትሆን ድረስ ተሸማቃለች ። እግዚአብሔር ልጅ የሚሰጠን ልጅ ያልወለዱትን እንድናሳቅቅበት አይደለም ፤ ልጅ ችሎታ ሳይሆን ስጦታ ነው ። እመ ሳሙኤል ሃና ለራስዋ ልጅን ስትመኝ ዘገየባት ፤ የዘገየው ልጅ ሲመጣ ግን ለእስራኤል ሕዝብ ትልቅ መልስ የሆነው ሳሙኤል ሆነ ። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ የወለዱትን ልጅ አላሳደጉትም ። በበረሃ ያደገው ዮሐንስ መጥምቅ ከመሸ የመጣ ነው ። የእነርሱ ደስታ የእግዚአብሔርን ክንድ ማየትና ነቀፌታቸው ሲወገድ መመልከት ነው ። ያልወለዱ የተመሰገኑበትና ብፁዓን የሚባሉበት ዘመን እንዳለ በማሰብ በመውለድ ብቻ መደሰት እንደሌለ እናስተውል ።

አዎ ልጅ ባትወልድም የምታየው ልጅ በሙሉ ያንተ ነው ። ብዙ ደናግልና መነኮሳት የብዙዎች አባትና እናት ናቸው ። እማሆይ ትሬሣን ታውቃቸዋለህ ። የሚሊየኖች እናት የሆኑ መነኵሲት ናቸው ። ልጅነት ብዙ እንደሆነ ፣ ወላጅነትም ብዙ ነው ። ይህ ዘመን የወለዱ ካልወለዱት በላይ የሚጨነቁበት ነው ። በአጭር ቃል ዘመኑ ልጅ ነጣቂ ነው ። ልጅ የወላጆቹን አሳብ ከሚያንጸባርቀው ይልቅ የዘመኑን አሳብ ማንጸባረቅ ይቀለዋል ። አውቃለሁ ባይነት ስለ ነገሠና በዕድሜ የገፉ የሚናቁበት ባሕል ስለ ተመሠረተ ወላጆች በልጆቻቸው ተከድተዋል ። ወላጅ ልጁን መገሠጽና መቅጣት የማይችልበት የሚያለያይ ዘመን ላይ ደርሰናል ። አዎ ልጆች ተሸማቀው ፣ እንዳይጠይቁ ተደርገው በፍርሃት ማደግ የለባቸውም ። በመኖር ፣ በማፍቀርም ከቀደሙአቸው ወላጆች ግን መማር አለባቸው ። ልጆች ቀለብ ከቤት ፣ ምክር ከደጅ ካደረጉ ቆይተዋል ። ወላጆቻቸውን አንሰማችሁም ተስፋ ቍረጡ እያሉ ነው ። አንዳንድ ጊዜ እኛም በወላጆቻችን ላይ የፈጸምነውን ዓመፃ በልጆች ልንቀበል እንችላለን ። ሌላ ጊዜም ልጅ እንደ ራሱ እንጂ እንደ እኛ አይደለም ። ነጻ ፈቃድ አለውና በራሱ መንገድ ቢሄድ የበደለኝነት ስሜት ሊያሰቃየን አይገባም ። የነቢዩ ፣ የቡሩኩ የዳዊት ልጆች አብዛኛዎቹ ክፉዎች ነበሩ ።

ልጅን ስለቀጣነው ብቻ አይታረምም ፣ ልጅ ከቃል ይልቅ በሕይወታችን የምናስተምረው አዳሪ ተማሪ ነው ። ልጅ ከእኛ ጋር ከሚያሳልፈው ዕድሜ ይልቅ ከሰፊው ዓለም ጋር የሚያሳልፈው ሰዓት ይበልጣል ። ንጹሕና ጉልበት ያለበት ሰዓቱን ቢያንስ ለስምንት ሰዓት በትምህርት ቤት ያሳልፋል ። ቤትን ከማሳመር አገርን ማሳመር ለልጆች ወሳኝ ነው ። አገሩ ከወደቀ ምንም ብንጠነቀቅ ልጆቻችን ገንዘብ አይሆኑንም ። አገርን እየዘረፈ ለልጆቹ የሚቀልብ ብዙ ወላጅ አለ ። በጉቦ ያደጉ ልጆች አእምሮአቸው ጤነኛ አይሆንም ። የሚበሉት ደም እንጂ እንጀራ አይደለምና ። የሰለጠነ አገር ልከን ብናስተምራቸው የሰለጠነ ሱስ ውስጥ ይገባሉ ።

የመጀመሪያ ልጅ የደስታችን መነሻ ነው ። ከዚህ በፊት በልጅ ተደስተን ስለማናውቅ የመጀመሪያው ልጅ ትልቅ ፍስሐ ያመጣልናል ። የመጀመሪያው ልጅ ከልምድ ማነስ የተነሣ በጣም ስለምንጠነቀቅለት ነጻነት የሚያጣ ይሆናል ። እርሱን የሚመስል ልጅ እቤት ውስጥ ስለሌለ ውሎው ከእኛ ጋር በመሆኑ ያለጊዜው ይበስላል ። ፍጹም እንዲሆን ወይም እንደ ትልቅ እንዲያስብ ስንፈልግ ብዙ ዱላ ልናበዛበት እንችላለን ። የመጀመሪያ ልጅ ፈሪ ወይም ቂመኛ መሆኑ የተለመደ ነው ። አሊያም የራሳቸው ጉዳይ ብሎ ቤተሰቡን ችላ የሚል ራስ ወዳድ ይሆናል ። ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ወላጅ ራሱን ቆጥሮ ቀንበር የሚሸከም ይሆናል ። ሁለተኛው ልጅ ሲመጣ ዓይን ሁሉ ከእርሱ ላይ ይነሣል ። በዚህ ምክንያት በቅንዓት ውስጡ ይጎዳል ። አልበላም እያለ የሚያምፀው የራሱን ጨርሶ የሌላውንም ቢበላ ደስ ይለዋል ። ራሱንም በገዛ ቤቱ ባዕድ ያደርጋል ። አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ልጆች ወላጆቻቸውን ክደው አባትና እናቴ አይደሉም እያሉ በደጅ ያወራሉ ። ፍቅር የተነፈጉ ፣ የመጀመሪያውን እንክብካቤ ያጡ ሲመስላቸው የደጅ ኀዘኔታ ለማግኘት በፈጠራ ታሪክ ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ ። የሚገርመው የፈጠራ ታሪካቸውን እያመኑት ይመጣሉ ።

የመጀመሪያ ልጅ ላይ ሥራ መሥራት ቀጣዮቹ እንዲባረኩ ያደርጋል ። ቀጣዮቹ ከወላጆቻቸው ይልቅ የበኵሩን ልጅ መከተል ይወዳሉ ። ስለዚህ የመጀመሪያ ልጅን ከመጠን በላይ መንከባከብ ተገቢ አይደለም ። ምክንያቱም አይዘልቅምና ። “የማይዘልቅ ጸሎት ለቅስፈት” እንዲሉ ። ይልቁንም በኵሩ የእግዚአብሔር ነውና ለእግዚአብሔር መስጠት ፣ አገልጋይ ማድረግ ይገባል ። በኵርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስንከለክል 12 ወልደን አንዱም የማይወደን እየሆነ መጣ ። ሰንበትን ለእግዚአብሔር ስንከለክል በሰንበት እየሠራንና እየተማርን በረከትና እውቀት የለሽ ሆንን ። እግዚአብሔርን ሰርቆ የበለጸገ ማንም የለም ።


ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.
Audio
የማርቆስ ወንጌል ትርጓሜ 25
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ማር . 6፣ 1-ፍጻሜ ዳሰሳ
እግዚአብሔር ይናገራል 7

በ#ዲያቆን #አሸናፊ #መኮንን የተዘጋጀ ስብከት

አሁን በቴሌግራም ቻናል ይለቀቃል ። ይከታተሉ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ትምህርቶችና ስብከቶች ለመከታተል ከሥር የተቀመጡትን ገጾች ይመልከቱ፡-

https://www.tg-me.com/Nolawi ኖላዊ/com.Nolawii

https://www.tg-me.com/nolawisebketoch

https://www.facebook.co m/ashenafi.mekonnen.357

https://youtu.be/3qfQp9yYmHY

www.ashenafimekonen.com
Audio
እግዚአብሔር ይናገራል 7

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ከፍ ካለው በላይ

የመጣው ሄደ፣ የሄደውም አይመጣም። የነገሠው ተሻረ ፣ የተሻረው ዳግም አይቀባም። የተሞገሰው ተረገመ፣ የተወገዘው ስሙ ያው ሆኖ ቀረ ። ባለ ጠጎች ደኸዩ ፣ አለ የሚባል ጠፍቶ ነበር የሚል ቃል በምድር በረከተ። ጎዳናው ይወስዳል ይመልሳል፣ ሕይወት ግን ያንን ጓደኛ፣ ያንን ውብ ዘመን፣ ያንን ክብር፣ ያንን አንቱታ አትመልስም ። በዘመኑ ታላቁ እስክንድር ዓለም ፈራው ፣ ዛሬ ፈሪዎች አይፈሩትም። እግዚአብሔር ማነው ? ያለው ፈርዖን ሰጠመ ፣ እስካሁን ትንሣኤ አላገኘም ። አውሮፓ ዱር ሳለ ግሪክ አሰለጠነች፣ ዛሬ ግሪክ በዕዳ ተዘፍቃ ብዙ ረዳት ሊያቆማት አልቻለም ። የጰጰሱ ተሳሳቱ ሲባል ይወገዛሉ፣ አስኬማና በትረ ሙሴ መልሱ ይባላሉ ።

ቆንጆዎች ቆንጆ ነበርሁ ሲሉ ማን ያምናቸዋል? ያ ውበት ላይመለስ ጥላሸት ተቀብቷል ። ያ ተክለ ቁመና ፣ ያ እንደ ፀሐይ የሚያበራ ገላ ፣ ያ መሬት ለመርገጥ የሚጸየፍ እግር ዛሬ ጭቃ ላይ ተኝቷል ። ቤቱን ለደቂቃ የማያምነው ለዘላለም ጥሎት ሄዷል። የሚሳሳለትን ንብረት ዛሬ የማያውቀው ሰው ይጫወትበታል ። የሕይወት መንገድ መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም ። እኛ ወደ እነርሱ እንጂ እነርሱ ወደ እኛ አይመጡም። የዓለም ከፍታ በዝቅታ ፣ ዙፋን በመቃብር ፣ ዳኝነት በእስረኛነት ይለወጣል ። ያንተን ልዕልና ፣ አማኑኤል ሆይ ያንተን ክብር ካላሰቡ ልብን ያደክማል ።

ከፍታህ ዝቅታ የለውም፡፡ ነበረ ተብሎ ታሪክ አይነገርልህም። ሁልጊዜ ያው ነህ ። እንዳንተ የሸመገለ የለም፤ እንዳንተም አዲስ የለም ። መጀመሪያ ላይ ቆመህ መጨረሻውን ታውቃለህ፤ እያወቅህ ግን ዝም ትላለህ። ለድሀው እንጀራ ትሰጣለህ ፣ መልሶ ሲክድህ የሚያማልድ ሰባኪ ትልክበታለህ ። በልካችን አትከፍለንም ፣ በልክህ ታኖረናለህ ። መሰላል ላይ የወጡ ይወርዳሉ። በአየር ላይ የተንሳፈፉ መሬት ይናፍቃሉ ። ከፍ ካሉት በላይ ከፍ ያልከው አንተ ግን በማይነገር ቅድስና ትኖራለህ ። ለጠባይህ ዝቅታ ፣ ለዙፋንህ መናወጥ የለበትም ። የዛሬው አሸናፊ የሁልጊዜ አሸናፊ አይደለም ። የዛሬው ፈራጅ የሁልጊዜ ፈራጅ አይደለም ። የእኔ አምላክ ግን የማለፍን ሥርዓት ድል ትነሣለህ ። ሳትቀበል ትሰጣለህ ። ሳትሾም ትሾማለህ ። አዎ ከፍ ካሉት በላይ ከፍ ብለሃል ። ልዕልናህን ልዕልናህ ያመሰግናል ። በክረምቱ ዝናብ ነጠብጣብ ልክ ብትመሰገን ልክህ አይደለም ።

በምድር ላይ ያንተ ትልቅ ነገር እኛ ነን ። በሰማይና በምድር የእኛ ትልቅ አንተ ሁንልን ! 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም .
የምእመናን ስሞች

በሚል ርእስ አራት ተከታታይ ትምህርቶች በየቀኑ ይለቃቃሉ ! እንድትከታተሉ ይሁን!





ዘመናችሁ ይባረክ!
Audio
የምእመናን ስሞች 1

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
Audio
የምእመናን ስሞች 2

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
2024/07/19 05:39:56
Back to Top
HTML Embed Code: